ታሪክን የኋሊት
- ethiosegenetmedia

- 5 days ago
- 1 min read

--
ኢ ሮ ብ
--
ኢሮብ በሰሜን ምስራቅ ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል ምስራቃዊ ዞባ የሚገኝና ከኤርትራ ጋር የሚዋሰን ብሄረሰብ የሚጠራበት ስም ነዉ፡፡
በጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ ሲገለጽ፤ የኢሮብ ህዝብ በሰሜን ምስራቅ በኩል ከሳሆ ብሄረሰብ፤ በሰሜን ምዕራብና በምዕራብ ከትግራይ ብሄረሰብ እንዲሁም በደቡብና በምስራቅ በኩል ደግሞ ከአፋር ብሄረሰብ ይዋሰናል።
ኢሮብ፣ በቀድሞው ዘመን የትግራይ ክፍለ ሀገር፣ አጋመ አውራጃ ውስጥ የምትገኝ ወረዳ ናት (በአሁኑ የአስተዳደር አወቃቀር በትግራይ ክልል፣ ምስራቃዊ ዞን ውስጥ ነው የምትገኘው)፡፡ በዚህች ወረዳ ከትግርኛ ተናጋሪው ብሄረ-ትግራይ በተጨማሪ ኢሮብ የሚባለው ብሄረሰብ ይኖራል፡፡ ይህ ህዝብ በውስጡ ሶስት ዐይነት ማህበረሰቦች አሉት፡፡ አንደኛው ደመክኒቶ ይባላል፡፡ የዚህ ማህበረሰብ አባላት የካቶሊክ ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ ሁለተኛው ማህበረሰብ “ሀሳበላ” የሚባል ሲሆን የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ይበዙበታል፡፡ ሶስተኛው ማህበረሰብ “ዳልገዳ” ይባላል፡፡ እነዚህኛዎቹ ደግሞ ሙስሊሞች ናቸው፡፡ እነዚህ ማህበረሰቦች የሚናገሩት ቋንቋ በኤርትራ ምድር ከሚነገረው የሳሆ ቋንቋ ጋር ተመሳሳይነት አለው፡፡ ሆኖም ኢሮብ እና ሳሆ በኢኮኖሚ ስምሪታቸው ይለያያሉ፡፡ የሳሆ ህዝብ ሙሉ በሙሉ አርብቶ አደር ነው፡፡ ኢሮቦች ግን በእርሻ ስራና በአነስተኛ ዕደ-ጥበባት ነው የሚተዳደሩት፡፡ የኢሮብ ወረዳ ተራራና ሸንተረር ይበዛዋል፡፡ በአካባቢው ካሉት ተራሮች መካከል “አሲምባ” እና “አይጋ” ትልልቆቹ ናቸው፡፡
ታዋቂ ግለሰብ፦ ከኢህአፓ መስራቾች አንዱና የድርጅቱ አውራ ታጋይ የነበረው ዶ/ር ተስፋዬ ደበሳይ የኢሮብ ብሔረሰብ ተወላጅ ነበር።
በምስሉ ላይ የኢሮብ ሰዎች በአንድ የዕርቅ ስነስርዓት ድግስ ላይ ለመገኘት ሌማቶችን ተሸክመው ወደ ስፍራው እያመሩ ነው።




Comments