ታሪክን የኋሊት!
- ethiosegenetmedia

- Dec 16, 2025
- 2 min read

---------------
በታህሳሱ ግርግር ያጣናቸው ዕንቁ ባለስልጣናት ......
ስመጥሩ አርበኛ ራስ አበበ አረጋይ
🟩🟨🟥
«ጠላት በአውሮፕላን በአየር ሲንደረደር
ያርበኞቹ መሪ ደባለቀው ካፈር
አንተ አበበ አረጋይ ፈረስህ ገስጥ
የፋሽስትን አንጎል እሚበጠብጥ፤»
ከብዙ የጀግንነት ታሪካቸው በጥቂቱ እንመልከት ፥የራስ ጎበና ዳጬ የልጅ ልጅ የሆኑት ራስ አበበ አረጋይ ከአባታቸው ከአፈ ንጉሥ አረጋይ ብቼሬና ከእናታቸው ወይዘሮ አስካለ ማርያም ጎበና ነሐሴ (14) ቀን 1896 ዓ.ም. በሰሜን ሸዋ ተወለዱ። ራስ አበበ አረጋይ የቤተክርስቲያንና ዘመናዊ ትምህርት በሚገባ ተከታትለዋል።
የራስ አበበ አያት ማለትም የወይዘሮ አስካለ ማርያም አባት ራስ ጎበና ዳጬ ናቸው በዳግማዊ ዓጼ ምኒልክ ዘመን የጦር አዝማች ሆነው ያን ጊዜ የተከፋፈለውን ህዝብ አንድ በማድረግ የታወቁ ዝነኛ ሰው የነበሩና የእምዬ ምኒልክ የቅርብ ወዳጅ ነበሩ።
ራስ አበበ አረጋይ ፋሺስት ኢትዮጵያን ከመውረሯ በፊት የክብር ዘበኛ ሻለቃ ነበሩ። ከዚያ ወደ ፖሊስ ተዛውረው ሃገራቸውን ሲያገለግሉ እንደቆዩ ጠላት አዲስ አበባ ሲገባ የበታች ጭፍሮቻቸውን አስከትለው የአበኝነት ተግባራቸውን ቀጠሉ።ከማይጨው ጦርነት ሽንፈት በኋላ ንጉሡ ወደ እንግሊዝ ሀገር በመሄዳቸው ጠቅላላ ወታደሩ በመበተን ወደ ሽምቅ ውጊያ ለመግባት ተገደደ። የራስ አበበም "እምቢ ለሀገሬ" የሚለው የአርበኝነትና የጀግንነት ውሎ የሚጀምረው ከዚህ ነው።
አበበ አረጋይ (በፈረስ ስማቸው አባ ገስጥ) የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ አንግበው አምስት ዓመት ሙሉ በሰሜን ሸዋ (በዱር በገደል) የኢትዮጵያን ሽምቅ ተዋጊዎች በመምራትና የኢጣሊያን ወራሪ ኃይል አሳፍረው በመመለስ ትልቅ ጀብዱ ፈጽመዋል። ከስድስት ጊዜ በላይም ቆስለዋል።
ከአምስት ዓመት የአርበኝነት ተጋድሎ በኋላ የፋሽስቱ ወራሪ ኃይል ሙሉ በሙሉ ተጠራርጎ ከኢትዮጵያ ሲለቅ ስደት ላይ የነበሩት አጼ ኃይለሥላሴ ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም. ወደ አዲስ አበባ ተመልሰዋል። በወቅቱ በራስ አበበ አረጋይና በሌሎችም የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ደማቅ አቀባበል ተደረጎላቸዋል። በዚህም ጊዜ ራስ አበበ አረጋይ ከወቅቱ የእንግሊዝ ጦር አዛዥ "የዘመናዊው ዓለም ታላቅ ጀግና" የሚል ዝናን አትርፈዋል።ፋሽስት ገና ስማቸውን ሲሰማ የሚደነብርላቸው ታላቅ ጀግና አርበኛ ነበሩ። ከዚህ በኋላም ለጥቂት ጊዜ የአዲስ አበባ ከንቲባ ሆነው አገልግለዋል።
በመጨረሻም ራስ አበበ አረጋይ ከ1948 እስከ 1953 ዓ.ም. የመከላከያ ሚኒስትር ሆነው ሀገራቸውን አገልግለዋል። በታሕሳስ ወር 1953 ዓ.ም. በአጼ ኃይለሥላሴ መንግሥት ላይ በወንድማማቾቹ መንግሥቱ ንዋይ እና ገርማሜ ንዋይ በተሞከረው መፈንቅለ መንግሥት ወቅት ራስ አበበን ከሌሎች ባለስልጣኖች ጋር እነ መንግስቱ ነዋይ በጥይት ገድለዋቸዋል። ከእነዚህ ባለሥልጣናት መላከል ራስ አበበ አረጋይ የክብር አክሊሉ ሀብተወልድ ወንድም አቶ መኮንን ሀብተወልድ ፣ የአፄ ዮሐንስ 4ተኛ የልጅ ልጅ ራስስዩም መንገሻ ይገኙበታል ። የታህሳስ ግርግር እጅግ አሳዛኙ ድርጊት አንዱ እነዚህ ባለስልጣናቶች በግፍ መገደላቸው ነው።
ራስ አበበ አረጋይ በተለይ በአምስት ዓመቱ የፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ ወቅት አርበኞችን አስተባብረው ለወራሪው የጎን ውጋት በመሆንና በማዳከም፤ በመጨረሻም ሀገራቸውን ኢትዮጵያን ነፃነቷን በማጎናፀፍ የሰሩት አኩሪ የጀግንነት ተግባር ሁሌም በታሪክ በደማቁ ሲዘከር ይኖራል።
በ5 ዓመቱ የጠላት ወረራ ጊዜ አርበኛና ጀግናው ራስ አበበ አረጋይ ( አባ ገስጥ ) ስለ አንድነታችን ከሚሰብከው ንግግራቸው በጥቂቱ :-
” ….በእርግጥ የሀገሬም ሆነ የማንነቴ አርማ ነውና ለዘውዱ እታመናለሁ ። ፈርቼና አጎብድጄ አላውቅም ። ዘመዶቼ መልካቸው ጠይም ፣ ቀይ ጠይም የቀይ ዳማ እና ጥቁር ናቸው ኦሮሞም አማራም ( ኢትዮጵያዊ ) ናቸው ። ሁሉም አፈር የሚገፉ ፤ ክፉውንም ደጉንም አብረው ያሳለፉ ።
መንዝ አመጸኛ ዋሻ የተሸሸጉትን ወገኖቼን ለመጨረስ መርዝ ጭኖ ሲበር የነበረውን የጠላት ጀት ጅሩ ላይ ሆኜ በረዥም ምንሽር ሞተሩን መትቼ በማጋየቴ ኩራት አይሰማኝም ። ጀግንነትም አይንጠኝም አላውቅም ምንም አይሰማኝም ።
ብቻ ለእኔ ” አረንጓዴ ፣ ቢጫና ቀዩን ” ባንዲራዬን ቀና ብዬ ስመለከት አንዳች ወኔ ውስጤን ይወረውና እምባ ይተናነቀኛል ። ምክንያቱን የሚገልጽ ቃል የለኝም ።
ወገኖቼ ኢትዮጵያ ያለ ፍቅር ፣ ያለ አንድነት ፣ ያለ መተሳሰብ ከቶውንም አትፀናም ። እናም እርስ በርሳችሁ ከልብ ተዋደዱ ። ”
ኢትዮ ሰገነት ሚዲያ




Comments