ታሪክን የኋሊት !
- ethiosegenetmedia

- Dec 14, 2025
- 2 min read

---------------
የወዝሊግ አመራር ከባድ ስህተት
➦➦➦➦
የወዝሊግ ድርጅት በቀላሉ ሥልጣን ለመጨበጥ የሚያስችል ሁኔታ የተፈጠረ መስሎት ለዚያ ግብ ያደርሰኛል ብሎ ያመነበትን ለየት ያለ ስልት ቀየሰ። ደርግን ተጠግቶና ደርግ በሚሰጠው ሁሉ አቀፍ ድጋፍ በመጠቀም ድርጅቱን ከማሳደግና ከማጠናከር አልፎ የደርግ መሪዎችንና አባላቱን በአባልነት በመመልመል ሥልጣን ለመጨበጥ ይቻላል ብሎ አመነ።
ሊቀመንበር መንግሥቱ ራሳቸው የሚመሩት የፖለቲካ ድርጅት እያደራጁ እንደሆነ የወዝሊግ መሪ ዶ/ር ሰናይ ሲያውቅ ቅሬታ ተሰማው። የሊቀመንበሩን ሃሳብ አልወደደውም። የእሱ ፍላጎት ሊቀመንበሩንና የእሳቸው ደጋፊዎች የነበሩ የደርግ አባላትን በእሱ ድርጅት ዙሪያ አሰባስቦ ድርጅቱን ወደ ከፍተኛ ደረጃ በማሳደግ ያለ ብዙ ችግር ሥልጣን ለመጨበጥ ቢሆንም የሊቀመንበሩ ሃሳብ ግን ፍላጎቱን በአጭር የሚቀጭ መስሎ ታየው።
በመሆኑም ገና በሃሳብ ደረጃ ላይ እንዳለ ለማምከን ሊቀመንበሩ በሃሳባቸው እንዳይገፉበት ለማግባባት ሞከረ። “ደርግ የፖለቲካ ድርጅቶችን እየደገፈና የፖለቲካውን መድረክ እያመቻቸ ሥልጣን እንዲረከቡ ከማድረግ ውጭ አባሎቹ ሌላ የፖለቲካ ድርጅት መመሥረት የለባቸውም። የራሳቸውን ድርጅት የሚመሠርቱ ከሆነ የቀሩት ድርጅቶች ይደክማሉ፣ የደርግ አባላት የፖለቲካው ተሳትፎአቸው እንዲጠበቅ ከተፈለገ በመረጡት የፖለቲካ ድርጅት አባል ሊሆኑ ይችላሉ” እያለ ሊቀመንበሩን ለማግባባትና ሃሳባቸውን እንዲቀይሩ ጥረት አደረገ። ሊቀመንበሩ ግን ሃሳቡን አልተቀበሉትም።
ሊቀመንበሩን ከአቋማቸው ሊመልሳቸው አለመቻሉን የተረዳው ዶ/ር ሰናይ አዲስ ይመሠረታል የተባለውን ድርጅት በማደራጀት ረገድ ቀረብ ብሎ መርዳት ይሻላል የሚል አማራጭ መንገድ ለመከተል ወሰነ። ይህን መንገድ ለመከተል የመረጠው በርግጥ ሊቀመንበር መንግሥቱ የሚመሠርቱትን ድርጅት ወድዶት ወይም አምኖበት ሳይሆን ድርጅቱን በመርዳት ስም የራሱን ድርጅት ለማጠናከር የሚችልበት ሁኔታ ያለ መስሎ ስለታየው ነበር።
ተፈጠረ ብሎ በገመተው ምቹ ሁኔታ በመጠቀም እሱ በሚመራው ወዝሊግ ድርጅት በአባልነት የተሰባሰቡ ወታደራዊ ካድሬዎችን መመሪያ በመስጠት ሊቀመንበሩ በሚያደራጁት ድርጅት ውስጥ በአባልነት እንዲመለመሉ አደረገ። እነዚህን ወታደራዊ ካድሬዎች ሕይወቱ እስካለፈበት ቀን ድረስ ለሊግ ድርጅት ሲያሠራቸው ቆየ። እሱ ከሞተ በኋላ ግን ብዙም ሳይቆይ ምሥጢሩ ተጋለጠ። የሰናይ ድርጊት ሊቀመንበሩን አስቆጣ። በመሆኑም በቅንነት የተመራ የሚመስለው ነገር ግን አርቆ አስተዋይነት የጎደለው የሰናይ አካሄድ፤ በሰደድ ውስጥ አስርጎ ባስገባቸው የሊግ አባላት ላይ የሞት አደጋ አስከተለ። የድርጅቱም ኅልውና በጥያቄ ውስጥ ወደቀ። የሊግ ድርጅት መሪዎች የሥልጣን ጉጉትም እንደጉም በነነ።
🔸እኛናአብዮቱ፤ፍቅረሥላሴወግደረስ ገጽ 352
ኢትዮ ሰገነት ሚድያ !




Comments