top of page
Search

ሰበር ዜና !

6 days ago
1 min read

በማረሚያ ቤት የሚገኙ ታራሚዎች '' ለወታደራዊ ዘመቻ እንዲሰለፉ'' እየተገደዱ መሆኑ ተገለፀ!



ኢትዮ ሰገነት ሚዲያ



በደቡብ ወሎ ዞን በደሴ ከተማ በሚገኘው ማረሚያ ቤት ውስጥ የሚገኙና ከዚህ በፊት መከላከያ ፣ ልዩሀይልና በሌሎች ወታደራዊ ዘርፎች ተሰማርተው ያገለግላሉ የነበሩ ታራሚዎች ብቻ ተመርጠው '' ለወታደራዊ ግዳጅ ስለምንፈልጋችሁ ራሳችሁን አዘጋጁ'' መባላቸውን ገልፀዋል። '' ካለፉት ጥቂት ሳምንት ወዲህ በተከታታይ በቡድንና በግል እየጠሩን ሀገር ልትወረር ነው ፣ ስለዚህ እናንተ ደግሞ ከዚህ በፊት ወታደሮች ስለነበራችሁ በቀጥታ ከመንግሥት ጎን ተሰልፋችሁ ለሀገራችሁ መዋጋት ይኖርባችኃል በማለት ለማሳመን ሲሞክሩ ሰንብተዋል'' የሚሉት ታራሚዎቹ ፣ የአመራሮቹን ሀሳብ የሚቀበልና ፈቃደኛ የሚሆን መጥፋቱን ተከትሎ ከፍተኛ ማስፈራሪያና ዛቻ እየደረሰባቸው መሆኑን አስታውቀዋል።



'' በቀደመው ህይወታችን በተለያዩ መስኮች ወታደራዊ አገልግሎት ስንሰጥ ከነበርነው መካከል አብዛሀኛዎቻችን በፍርድቤት ውሳኔ ተወስኖብን በእስር ላይ የምንገኝ ነን'' የሚሉት ታራሚዎቹ ፣ በፍርድ ሂደት ላይ የሚገኙና በጊዜ ቀጠሮ ላይ ያሉ እንዳሉም ጠቁመዋል። ከአለምአቀፍ የሰብአዊ መብትና የእስረኛ አያያዝ ህግጋት በሚፃረር መልኩ 'በአስገዳጅ ሁኔታ ለወታደራዊ ግዳጅ ትሰማራላችሁ' የሚለውን የአገዛዙ አካሄድ በፅኑ የኮነኑት ታራሚዎቹ '' መንግስት የፍርድ ጊዜአችንን ጨርሰን እስከምንወጣ በህግ በተደነገገው አግባብ እንደእስረኛ ሁለንተናዊ መብታችንን አክብሮና አስከብሮ ሊጠብቀን ሲገባ ለጦርነት አሰልፋችኃለሁ ማለቱ ፍፁም ሀላፊነት የጎደለው ተግባር ነው'' ሲሉ ገልፀዋል።



'' ከወር በፊት ከደሴ ማረሚያ ቤት በልዩ ልዩ ወታደራዊ ተቋማት ስናገለግል የነበርንና ወደ400 የምንሆን ታራሚዎች ተመርጠን ወደሌላ ቦታ ልንወስዳችሁ ነው ተዘጋጁ ተብለን እኛን ጨምሮ ቤተሰብቻችንም ሲጨነቁ ሰንብተዋል'' የሚሉት ታራሚዎቹ ፣ '' ሰሞንኛውን ሁኔታ ተከትሎ አንዳንድ ታራሚዎች እየተመረጡ በፀጥታ ሀይሎች ከታሰሩበት ቦታ ተወስደው ድብደባና አካላዊ ጥቃት እየደደረሰባቸው መሆኑን'' ጠቁመው ፥ በዚህ ምክንያትም በከፍተኛ ጭንቀትና ስነልቦናዊ ጫና ውስጥ እንደሚገኙ ገልፀዋል!



ኢትዮ ሰገነት ሚዲያ

 
 
 

Comments


bottom of page